ለጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ

ግንቦት 11/2013 (ዋልታ) – በተመድ የስነ ሕዝብ ፕሮግራምና የኮሪያ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸውን የሕክምና ቁሳቁስና አምቡላንስ ለጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ድጋፍ አደረገ።

በተባበሩት መንግስታት የስነ ሕዝብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ዲኒያ ጋየል በዲላ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድጋፉ በጤና ተቋማት ውስጥ በወላድ እናቶችና በሕጻናቶች ላይ የሚያጋጥመውን የጤና ችግር ለመቅረፍ የሚያግዝ ነው።

ድጋፉ ለወላድ እናቶች አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት አምቡላንሶች፣ መድሃኒት እንዲሁም የተለያዩ የህክምና ግብዓቶቸን ያካተተ መሆኑን ተናግረው፣ ለተደረገው ድጋፍ ከ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።

የኮሪያ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተወካይ አቶ ጌታነህ አሰፋ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ የወጣቶችን ስነ ተዋልዶ ጤና እንዲሁም የሕጻናትና የእናቶች የጤና ስርዓት ለማዘመንና የሚገጥሙ የሕክምና ግብአቶች ችግር ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ ጠቁመው፣ በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰል ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ ድጋፉ ሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፣ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት ደግሞ የምዕራብ ጉጂ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሳሊ ቂልጣ ናቸው።

በተለይ ከሕክምና ግብአቶች በተጨማሪ በወጣቱ ትውልድ ላይ እየተሰራ ያለው የስነ ተዋልዶ ግንዛቤ ማስጨበጥና የገንዘብ ድጋፍ በጤናው ዘርፍ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ እገዛ ማድረጉን አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።