የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳሰበ

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማደናገር የሞከሩ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳሰበ፡፡

ሰሞኑን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ያላግባብ ተጠቅመው አገልግሎቱን በተመለከተ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማደናገር ሲሞክሩ የነበሩ አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች ከህገወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ተቋሙ አሳስቧል፡፡

አገልገሎት መሥሪያ ቤቱ ከዚህ በኋላ የሀሰት መረጃዎችንና አሉባልታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማሰራጨት የሀገርን ብሄራዊ ጥቅምና ህልውና ለመጉዳት እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ማስረጃዎችን በማጠናቀር በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሀገር ላይ የሚቃጡ የፀጥታና የደህንነት ስጋቶችን በማስቀረት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከማንኛውም ጊዜ በላይ ከሁሉም የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ መግለጫው አመልክቷል።