የተፈናቀሉ ዜጎች በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉበት አሰራር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ”ይጠይቁ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የማህበራዊ ሚዲያ የተሳትፎ መድረክ ለቀረቡ ጥያቄዎች በቦርዱ የፌስቡክ ገጽ በቀጥታ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎች በምርጫው በምን አይነት መልኩ ይሳተፋሉ? በሚል ከተሳታፊ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የተፈናቀሉ ዜጎች በምርጫው ላይ የሚሳተፉበትን ሁኔታ ቦርዱ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ዜጎቹ ባሉበት ቦታ ሆነው የሚመዘገቡበትና ከመጡበት አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ምርጫውን የሚያደርጉበት ሁኔታ መመቻቸቱን አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ የተፈናቀሉት ዜጎች የሰጡትን ድምጽ ከመጡበት አካባቢ ሰዎች ከሚሰጡት ድምጽ ጋር የሚደመርበት የውጤት ማስላት ዘዴ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በአዲስ መልክ ዜጎች የተፈናቀሉባቸው ቦታዎች በመኖራቸው የወቅቱን መረጃዎች ማወቅ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
“ለዚህ ደግሞ የሰላም ሚኒስቴርና የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የሚያወጧቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎች ባሉባቸው አካባቢዎች ለመራጮች ትምህርት ለመስጠት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና ሌሎች በተጓዳኝ የሚከናወኑ ስራዎች የሚመሩበት እቅድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ባወጣው የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ ግንቦት 28 ቀን 2013 አጠቃላይ የመራጮች ድምጽ መስጫ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።