የካቲት 05/2013 (ዋልታ) – በካናዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ የሚገኘውን የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴና የሰብአዊ ድጋፍ ለካናዳ ምክር ቤት አባል ገለጹ።
አምባሳደሩ ከካናዳ ምክር ቤት አባል ግራኔት ጄኑስ ጋር በነበራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል ስለተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴና የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ በተመለከተ በሰፊው አብራርተዋል።
መንግስት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በማክበር እና በአካባቢው ያሉ ንጹሃንን በመጠበቅ ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት።
የካናዳ ምክር ቤት አባል ግራኔት ጄኑስ በበኩላቸው፣ መንግሰት እያካሄደ ያለውን የመልሶ ግንባታና የድጋፍ እንቅስቃሴ አድንቀው ካናዳ የኢትዮጵያ ጠንካራ የልማት አጋር መሆኗን አስታውቀዋል።
በሰብአዊ ድጋፍና በመልሶ ገንበታ ስራዎችም የካናዳ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ሆኖ እንዲሰራ እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተዋል።
በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ወቅት የታዩ ብዥታዎችንና የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማረምም ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ሆነው እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።