መጋቢት 04/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ምክር ቤት 17ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን ሠንደቅ ዓላማና ዓርማ ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡
ምክር ቤቱ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ የክልሉን ሕዝብ ሊወክል የሚችል ሠንደቅ ዓላማ ተጠንቶ እንዲቀርብ ወስኗል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የህግ አማካሪ አቶ አለልኝ የኋላ የማሻሻያ አዋጁን ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ ሠንደቅ ዓላማውን መቀየር ያስፈለገው የክልሉን ሕዝብ ባህልና ወግ የማይወክልና በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያጣ በመሆኑ ነው፡፡
በወቅቱ ነባሩን ሠንደቅ ዓላማ በአዋጅ ሲጸድቅም የክልሉ ሕዝብ ሃሳብ ያልሰጠበትና ያልተሳተፈበት በመሆኑ የእኔ ነው ብሎ ሳይወስደው ተገዶ የተጫነበትመሆኑን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ በበኩላቸው የክልሉን ሕዝብ ሥነ ልቦና ሊወክል የማይችል ሠንደቅ ዓላማ እንዲኖር ህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ግፊት ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
የክልሉን ሕዝብ ሊወክል የሚችል ሠንደቅ ዓላማ በአጭር ጊዜ ተጠንቶ እንዲቀርብ የተወሰነውም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ አጥኚ ኮሚቴ በማቋቋም እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
“እስካሁን ስንጠቀምበት የቆየነው ሠንደቅ ዓላማ የሕዝቡን ወግና ባህል የማይመጥን በመሆኑ መቀየሩ ተገቢ ነው” ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል አቶ ወርቁ ኃይለማርያም ናቸው፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ንጉሴ ዓለሙ በበኩላቸው ነባሩ ሠንደቅ ዓላማ እኛን አይወክልም በሚል ህዝቡ ቅሬታ ሲያነሳ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡን የሚወክል ሠንደቅ ዓላማ በአጭር ጊዜ ተጠንቶ ሊቀርብና በምክር ቤቱ ጸድቆ ሥራ ላይ ሊውል እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ምክርቤቱ የቀረበው የማሻሻያ አዋጅ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ የክልሉን ሕዝብ ታሪክ ባህል እና ሥነ ልቦና ሊወክል የሚችል ሠንደቅ ዓላማ በሚቋቋመው ኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብም በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በባህርዳር ከተማ ዛሬም ቀጥሎ ያለው የምክር ቤቱ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ኢዜአ ዘግቧል።