የአቃቂ ጨፌ ፍሳሽ ማጣሪያና ቁጥጥር ላቦራቶሪ አስተዳደር ህንፃ ተመረቀ

ሚያዝያ 20/2013 (ዋልታ) – በአቃቂ እና ቃሊቲ የተገነቡትን የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን ጨምሮ የፍሳሽ ቁጥጥር ላቦራቶሪ አስተዳደር ህንፃ ፕሮጀክቶች ተመረቁ፡፡

በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ሶስቱም ፕሮጀክቶች በከተማ አስተዳደሩ አቅም የተሰሩ ሲሆን ጠንካራ የክትትልና ግምገማ ስራ መሰራቱ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አድርጓል።

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ይሸፍናል የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለፁት ከንቲባዋ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋለውን ማነቆ የማቃለል አቅም እንዳላቸው ግን ገልጸዋል፡፡

ሶስቱም ፕሮጀክቶች በ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ ሲሆን 25 ሺህ በላይ ኪዩቢክ ሜትር ፍሳሽ የማጣራት አቅም አላቸው ተብሏል።

የመዲናዋ የፍሳሽ ማጣራት አቅም በቀን ወደ 148 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ብሏል ተብሏል።

በምረቃ ዝግጅቱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት ሰጪ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራል ዓባይ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
(በደረሰ አማረ)