የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀለኞችን አድኖ የመያዝና የመልሶ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙት የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ከሃዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መንግስት የህግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻ በማድረግ እና በድል በማጠናቀቅ የጁንታውን አባላት አድኖ የመያዝ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

“የጁንታው ቡድን በተላላኪዎቹ አማካይነት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ግጭት እንዲፈጠር እና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ከተረጋገጠ በኋላ በአዲስ አበባም ይህ የጥፋት ተልዕኮ እንዳይሳካ ለማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባከናወነው ልዩ ልዩ ተግባር ለጥፋት አላማ ሊውሉ የነበሩ በርካታ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና የከተማችንን ሰላም አስጠብቆ ቀጥሏል” ብሏል።

በህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ የተሳተፉ እና ጉዳት የደረሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ለመደገፍ እንደሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ሁሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራር እና አባላት እንዲሁም ሲቪል ሰራተኞቹን ጨምሮ ደም የመለገስ ተግባር ማከናወናቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የፖሊስ ኮሚሽኑ አመራር እና አባላት ከተሰጣቸው ህግን የማስከበር ተልዕኮ ጎን ለጎን ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚያሳዩትን አጋርነት አጠናክረው በመቀጠል ሲቪል ሰራተኞቹን ጨምሮ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

በዚህም በተቋሙ ሰራተኞች ስም ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መደረጉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።