ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ፖሊስ በአስተሳሰብ የለውጥ ማዕከል የተቋሙን አቅም በማሳደግ ላይ ተመስርቶ ገለልተኛነቱን የሚያረጋግጥ የሪፎርም ተግባር ማከናወኑን የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ ፖሊሳዊ የደንብ ልብስ እና ዓርማ የማብሰሪያ መርሀ-ግብር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
በማብሰሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሯ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሥርአት አገልጋይነት የህዝብና የሀገር አገልጋይ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ እየተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት የፖሊስ ተቋም ለውጥ ሲካሄድ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስም በአስተሳሰብ የለውጥ ማዕከል የተቋሙን አቅም በማሳደግ ላይ መሰረት ያደረገ ገለልተኛነቱን የሚያረጋግጥ ተግባር እንዳከናወነ አብራርተዋል፡፡
ይህን በሚያረጋግጥ መልኩ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፌደራል መከላከያ ኃይል፣ ከሌሎች የጸጥታና ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን በፈታኝ ወቅት ጭምር ሥርአትን ሳይሆን ህዝቡንና ሀገርን ያስቀደመ ተግባር ማከናወን መቻሉን አንስተዋል፡፡
ለውጡ ፖሊስ ተፈርቶ ሳይሆን በህዝብ ዘንድ ተወዶ የሚከበር እንዲሆን ያስቻለ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ሙፌሪሃት፣ የአዲስ አበባን የፖሊስ ተቋም በዘመናዊ የሰው ሃይል፣ አስተሳሰብ፣ ስልጠናና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ “ይህም ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እንዲወጣ ያስችለዋል” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰአትም ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ባህሉን እያደገ እንሚገኝም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡