የአዲስ ዋልታ አዲስ መንገድ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 30/2015 (ዋልታ) የአዲስ ዋልታ አዲስ መንገድ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ሪፎርም ላይ የሚገኘው ዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት በዛሬው ዕለት አዲሱን ዓርማ (ሎጎ) በማስተዋወቅ ላይ ነው የሚገኘው፡፡

በዚህም ተቋሙ ከዚህ በፊት በህዝብ ዘንድ የሚታወቀውን ስም “ዋልታ”ን አሁን ላይ ወደ “አዲስ ዋልታ” መቀየሩም ተገልጿል፡፡

በዚህ የማስተዋወቂያ መርኃ ግብር ላይ የአዲስ ዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ቦርድ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ላለፉት ረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ በርካታ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ለአድማጭ ተመልካቾች እያደረሰ የሚገኘው ተቋሙ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በዜና፣ ፕሮግራም እንዲሁም ዶክመንተሪ ስራዎችን በማቅረብ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘ ተቋም እንደሆነም ይገለፃል፡፡

ታዲያ ይህንንም ለማስፋፋት በማለም ባለፉት ወራት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ከአመሻሽ እስከ ምሽት፣ ሰላም ኢትዮጵያ በሚል እንዲሁም በሌሎች መርኃግብሮች የተለያዩ መረጃዎችን ለተመልካቾች እያደረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡