የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ አደረገ

ነሐሴ 5/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 1/2015 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የዋጋ ንረትን ሊቀንሱ የሚችሉ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የባንኩ ገዢ ማሞ ምህረቱ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው የዋጋ ንረት በህብረተሰባችን ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽል ቁጠባና ኢንቨስትመንት የሚበረታታበት እንዲሁም የስራ ዕድል የሚፈጠርበት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚረዳ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት የዋጋ ንረትን ሰኔ መጨረሻ ላይ ከ20 በመቶ በታች በ2017 ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በያዝነው በጀት ዓመት ባንኩ ለመንግስት የሚሰጠው የቀጥታ ብድርን በመቀነስ ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ብድር ከአንድ ሦስተኛ እንዳይበልጥ በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስቴር ቀጥታ ብድርን እንደ መጨረሻ አማራጭ የሚጠቀመው የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ በበቂ መጠን ለገበያ መቅረብ ሳይይችል ሲቀር ብቻ እንደሆነ ከመግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሄራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ከ16 በመቶ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋልም ነው የተባለው።

የውጭ የንግድ ዘርፎች በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታታት የውጭ ምንዛሪን የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል እንደሚደረግም ተመላክቷል።

በመቅደስ የኔሁን