የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት 11ኛው ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ

መስከረም 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት “ደም ይለግሱ፣ ህይወትን ያጋሩ፣ ብርሀንን ይስጡ፣ እይታን ይመልሱ” በሚል መሪ ቃል 11ኛው ዓመታዊ ጉባኤውን በሀረር ከተማ አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት በቂ እና ጥራቱን የጠበቀ ደም ለጤና ስርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ባንኩ ደም በመሠብሠብ፣ በመመርመር፣ በማከማቸት እና በማሠራጨት ረገድ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ አደራጃጀቱን የማጠናከር፣ አሠራሩን በማሻሻል ህብረተሰቡን ባለቤት አድርጎ ለመስራት ግንዛቤና ንቅንቄ ለመፍጠር፣ ሚድያዎችን በመጠቀም ረገድ ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ 490 ሺሕ 699 ዩኒት ደም ለመሠብሠብ ታቅዶ 352 ሺሕ 908 ዩኒት ደም መሠብሠቡን ገልጸው ከ19 ሺሕ በላይ የድህረ ምክር አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

የሀረሪ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኤልያስ ከ50 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት ታሪክ ሀረር ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የደም ባንክ የተጀመረባት ሁለተኛ ከተማ መሆኗን ገልጸው መድረኩ የደም ባንኮች በደም አቅርቦት አፈጻጸም እና በሌሎች ተግባራት ልምድ የሚቀሰምበት መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ዳራዊ ሁኔታ አሁን የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ እንዲሁም የአይን ብሌን ማሰባሰብ ላይ የህብረተሠቡ ተሳትፎ የሚያሳይ ኤግዚብሽን ቀርቧል።

የ2015 በጀት ዓመት ጥሩ አፈጻጸም ለነበራቸው ደም ባንኮች፣ ክልሎች እውቅና የሰጠ ሲሆን አርቲስት ይገረም ደጀኔን እና አርቲስት ሸዊት ከበደ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አምባሳደር አድርጎም መሾሙን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።