የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በአሸባሪው ሕወሓት ወድሟል፤ ተዘርፏል

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እያንዳንዱ ንብረት በአሸባሪው ሕወሓት ተዘርፏል፤ ቀሪው አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኖ ወድሟል።

አሻባሪው ሕወሓት በወልዲያ እና አካባቢው በወረራ በቆየባቸው ወራት ዩኒቨርሲቲውን ጨምሮ በርካታ የሕዝብና የግለሰብ ንብረቶችን ዘርፏል፤ ያልቻለውን አውድሟል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማጣቱን ገልጸው አሸባሪ ቡድኑ የዩኒቨርሲቲውን ቢሮዎች ክፉኛ ሰባብሯል፣ የላብራቶሪ እቃዎች እና ኮምፒውተሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ገስት ሀውስ፣ አይሲቲ ክፍሎች፣ ላይብረሪና ኢ-ላይብራሪ ህንፃውና በውስጡ የነበሩ ንብረቶች ዘረፋና ከፍተኛ ውድመት ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።

ሆኖም የዩኒቨርሲቲውን መሰረታዊ መማር ማስተማር በሂደት ለማስጀመር የሚያስችል መርሃ ግብር ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያዊያን የሚማሩባቸውን፣ የሚታከሙባቸውን እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኙባቸውንና ሰርተው ኑሯቸውን የሚደጉሙባቸውን ፋብሪካዎች ጭምር በመዝረፍና በማውደም የክፋት ጥጉን አሳይቷልም ነው ያሉት።

ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት የሰሩና የተማሩ ጭምር የአሸባሪው ቡድን አባል በመሆን “የበሉበትን ወጭት ሰባሪ” ሆነው መገኘታቸውን አረጋግጠናል ሲሉም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አክለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ላይ የተፈፀመው ዘረፋና ውድመት የከፋ ቢሆንም የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።