የውጪ መገናኛ ብዙሀን በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተዛባ መረጃ እያሰራጩ ነው

በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ የውጪ መገናኛ ብዙሀን  ስራቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከመስራት ይልቅ በጥቅም የተሳሰሩ አካላት የሚሰጡዋቸውን መረጃ እውነትነት ሳያረጋግጡ እያቀረቡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው ምሁራን የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራው ባለው የዲፕሎማሲ ስራ  እውነታውን ለአለም እያሳወቀ በመሆኑ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰው አሁንም ያለውን መረጃ በወቅቱ ማድረስ ላይ የተጠናከረ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ጥቂቶቹ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሚዛናዊ ና ትክክለኛ መረጃን ለማድረስ ሲሞክሩ በርካቶች ደግሞ ከእውነት የራቀና የራሳቸውን መላምት የሚመስሉ ዘገባዎችን እያሰራጩ ነው ተብሏል፡፡

መንግስት በሰራው እውነታውን ለአለም የማሳወቅ ዲፕሎማሲያዊ ስራ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀኑ መጠነኛ ማሻሻያ ቢያሳዩም አሁንም አጀንዳዎችን እየቀረጹ ጉዳዩን የተለያየ ምልከታ እንዲሰጠው እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት እውነታውን ለአለም የማሳወቅ ስራ መስራት በመቻሉ በጉዳዩ ላይ መጠነኛ ለውጥ መጥቷል ያሉት ምሁራኑ አሁንም የደረሰበትን ወቅታዊ ሁኔታ በወቅቱ እና በስፋት መረጃዎችን የመስጠት ስራ መስራት አለበት ብለዋል፡፡

እንዲሁም አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀኑን  ህግ የማስከበር ዘመቻው የተካሄደበትን ቦታ ወስዶ ያለበትን ሁኔታ ሊያስመለክታቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በመስከረም ቸርነት