የዓድዋ ድል የአልገዛም ባይነትና የአንድነት ምልክት መሆኑ ተጠቆመ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የዓድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያዊያን የጀግነነት፣ የአልገዛም ባይነት እና የአንድነት ምልክትና ኩራት መሆኑን ገለጸ።

የክልሉ መንግሥት ለ126ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም ድሉ የቅኝ ገዥዎችን እብሪት የሰበረ፣ በተቃራኒው የቅኝ ተገዥዎችን የነጻነት ትግል ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀና በተለይም በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ይቻላል የሚል እሳቤ የፈጠረ ፈር ቀዳጅ ድል ነው ብሏል።

እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የአንድነታችን ማሳያ የትብብራችን ውጤት የሆነውን ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በጀመረበት ዋዜማ መከበሩ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል ልዩ እንደሚያደርገው ተመላክቷል።

ድህነትን ለማሸነፍ በአንድነትና በአልሸነፍ ባይነት በመዝመት የተሻለች አገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ መግለጹንም ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።