ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እኩል ደረጃ ያላቸው አራት ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት የክልሉ ምክር ቤት አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው የብዝኃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከክልሉ ስድስቱም ዞኖች ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።
የብዝኃ ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቦንጋ፣ ተርጫ፣ ሚዛን አማን እና ቴፒ እኩል ደረጃ ያላቸው የክልሉ ዋና ከተሞች ይሆናሉ ይላል።
ቦንጋ ከተማ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳደሩ መቀመጫ፣ ታርጫ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ፣ ሚዛን አማን የዳኝነት አካል መቀመጫ እንዲሁም ቴፒ የብሔረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫ እንደሚሆኑም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።
የክልሉ ዋና ከተሞች አራት እንዲሆኑ የተደረገው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ እንደሆነም የብዝኃ ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ ይጠቅሳል።
ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ በክልሉ ምክር ቤት ፀድቆ የሚተገበር ከሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እኩል ደረጃ ያላቸው አራት ዋና ከተሞች ያሉት የመጀመሪያው ክልል ይሆናል ተብሏል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የክልሉ ዋና ከተሞች አራት እንዲሆኑ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተጨማሪ ውይይቶች ሊደረጉ እንደሚገባ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወንድሙ ኩርታ በመሩት መድረክ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ሥልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም ውይይት እንደተደረገበት የኢብኮ ዘገባ አመላክቷል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW