ግንቦት 11/2013 (ዋልታ) – የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከማብቃት ባሻገር ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ እንደሚገኝ ገለፀ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተሰማ ዘውዱ (ፕ/ር) በጥናትና ምርምሩ ዘርፍ የማህበረሰቡን ችግር ይፈታሉ የተባሉ የብዝሀ ህይወት፣ ግብርና እንዲሁም ቱሪዝም ዘርፍ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸው በተጓዳኝ በአካባቢያቸው ያለውን ችግር ለይቶና ማኅበረሰቡን አማክሮ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምርን የማድረግ ተልዕኮ እንደለባቸው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ተሰማ፣ ዩኒቨርሲተው መፍትሔ የሆኑ ጥናትና ምርምሮች እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በ2010 የተቋቋመውና የ4ኛው ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እየተባለ የሚጠራው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር በመሆን የአጭርና የረዥም ጊዜ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ባሻገር በአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በበጋ የመስኖ ግብርና ጥቅም ላይ የሚውሉና የአርሶ አደሩን ህይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ምርምሮች ላይ ትኩረት ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡
(በዙፋን አምባቸው)