የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት የተፈጥሮ ጸጋዎችን ወደ ልማት መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ነው

መስከረም 19/2016 (አዲስ ዋልታ) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ልማት መቀየር እንደሚቻል ማሳያ መሆኑ ተገለጸ።

የዓለም ቱሪዝም ሳምንትን በተመለከተ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮንታ ዞን የመስህብ ሥፍራዎች ጉብኝት ተካሂዷል።

በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ የተመራው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ቡድን በኮንታ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ኮንታ ዞን በቱሪዝም ልማት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥፍራዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው መንግሥት ይህን ኃብት ለማስተዋወቅ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በገበታ ለሀገር የአካባቢው ማኅበረሰብ ባህላዊ ሃብቶች የሚተዋወቁበት ይሆናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በመንግሥትና በግል ባለሃብቶች እየተገነቡ ያሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።

ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ 4 ሺሕ 100 ሄክታር የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም ትልልቅ ወንዞች፣ ሐይቆችና ፏፏቴዎችን ያቀፈ መሆኑ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ የአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት የፍራፍሬና የቅመማቅመም ዕምቅ አቅምን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።

የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት በተፈጥሮ ውበት የቸረውን መልክዓ-ምድር በጥቂት ኢንቨስትመንት ወደ ጥቅም መለወጥ እንደሚቻል የሚያሳይና ሌሎችም በዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲነሳሱ የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ በጉብኝታቸው ወቅት አመላክተዋል፡፡

የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክም በተፈጥሮ ሕብር የሚታይበትና የቱሪስት ቆይታ የሚያራዝም መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነጋ አበራ በዞኑ የሚገኘው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ ሐይቆች፣ ፏፏቴዎች፣ ጥብቅ ደኖችና በዕፅዋት ብዝኃ-ሕይወት እንዲሁም የተለያዩ የዱር እንስሳት የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ ወዲህ የቀድሞው የኮንታ ልዩ ወረዳ ወደ ዞንነት ከማደጉ ባሻገር በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚነትን የሚጨምሩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

የገበታ ለሃገር ፕሮጀክትም በዞኑ መተግበሩ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከገበታ ለሃገር ኮይሻ ፕሮጀክት በተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻና ማረፊያ ቦታዎቹ እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የኅብረተሰብን ባህላዊ እሴት ለማስተዋወቅና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያጎለበተ መሆኑን አንስተዋል።

የመንገድና መሰል መሰረተ-ልማቶች የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያመጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሁንም ውስንነት እንዳሉበት ገልጸው ከቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሳራ ስዩም (ከኮንታ ዞን)