የጉሙሩክ ኮሚሽን በ2013 በጀት አመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለመሰብሰብ ካቀደው 58 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ውስጥ 55 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር መሰብሰብን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ የ2013 በጀት አመት የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጆችና አመራሮች በተገኙበት ግምገማ አካሂዷል፡፡
በዕቅድ ግምገማው ላይ የተገኙት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በ2013 በጀት አመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለመሰብሰብ ካቀደው 58 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ውስጥ 55 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል፡፡ የዕቅዱን 94 ነጥብ 95 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል፡፡
የገቢ አሰባሰቡ በእቅድ ከተያዘው አንጻር ጉድለት ቢኖርበትም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል፡፡
በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከዕቅድ አንፃር የታየውን የገቢ ጉድለት በቀሪ ወራቶች ለመሰብሰብ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ርብርብ ማድረግ ይገባቸውዋል ያሉት አቶ ደበሌ፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሚታየው የአፈፃፀም ልዩነት ለማጥበብ ጉደለቶችን ለይቶ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
በቀሪው 6 ወራት ህግን የማስከበር ስራ በተጠናከረ ሁኔታ የሚሰራበት ጭምር መሆኑን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡