ጆ  ባይደን ጥቁር አሜሪካዊውን ሎይድ ኦስቲንን እጩ የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው መረጡ

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቁር አሜሪካዊውን የቀድሞ ጀነራል ሎይድ ኦስቲን እጩ የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው መረጡ።

በኦባማ አስተዳደር ወቅት የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድን የመሩት ሎይድ ኦስቲን ጡረታ ከወጡ ሰባት አመት ያልሞላቸው በመሆኑ የኮንግረሱ ይሁንታ ያስፈልጋቸዋል ነው የተባለው።

ጆ ባይደንም ሆነ ሎይድ ኦስቲን በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት ባይሰጡም የ67 ዓመቱ የቀድሞ ጄነራል በመከላከያ ሚኒስትርነት ፔንታገንን የመሩ የመጀመሪያው አፍሪካዊ- አሜሪካዊ ይሆናሉ።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ደህንነት ቡድን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ይፋ ካደረጉ  ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው የመከላከያ ሚኒስትር ምርጫ ያካሄዱት ተብሏል።

የወቅቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በምርጫ ያሸነፉት ባይደን በስልጣን ዘመናቸው ብዝሃነትን የምታስተናግድ አሜሪካን ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረው ነበር።

ለዚህም ከወዲሁ እያካሄዱት ለሚገኘው የተለያዩ ቦታዎች  ውስጥ ለሴቶች፤ለጥቁሮች ፤ላቲኖች እና ሌሎች በከፍተኛ የካቢኔ ቦታዎች ላይ  ሹመት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በአወዛጋቢው የአሜሪካ ምርጫ ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑት ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል እንዳሉ  ቀጥለዋል።

ሎይድ ኦስቲን ኢራቅ  የነበረው ሰራዊት የአሜሪካ ጦር ኃይሎች የመጨረሻው አዛዥ ጄኔራል ሆነውም አገልግለዋል፡፡

በኢራቁ ተልጽኮ ወቅት የባራክ ኦባማ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ከነበሩት  ጆ  ባይደን ጋር በቅርበት ሰርተዋል ነው የተባለው፡፡

የትራምፕ አስተዳደር የወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ሚለር ሲሆኑ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፉት አራት አመታት ውስጥ ስድስተኛ የመከላከያ ሚኒስትር ሹመት ሰጥተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡