ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው ከፈቱ።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር እና ሌሎችም ከፍተኛ የፌደራል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በፌደራል ደረጃ ሞዴል ተብለው ከተመረጡት አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታው የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነበር፡፡
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዛሬ የተመረቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ በ260 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው፡፡
እስካሁን ባለው የግንባታ ሂደት 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጭ የተደረገበት ይህ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ100 ኪሎ ሜትር ራዲየስ 7 መጋቢ የገጠር የሽግግር ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ያቀፈ ነው፡፡
ሞጣን ጨምሮ ከአማኑኤል እስከ ፍኖተ ሰላም፣ ከዳንግላ እስከ መርዓዊ፣ ከእንጅባራ እስከ ቻግኒ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መጋቢ ማዕከላት ሆነው ያገለግላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
(በምንይሉ ደስይበለው)