ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀመሩ

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ሰኔ 16/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት ከሪፐብሊካን የጥበቃ ሀይል ጋር በመሆን አራት ኪሎ በተለምዶው አዋሬ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው መንደር ነው የበጎ ፈቃድ አግልግሎት መርሃግብሩን ያስጀመሩት።

በዘንድሮው ክረምት በዚሁ መርሃ ግብር ከ10 እስከ 15 ቤቶችን ለማደስ እንደተዘጋጁ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ 7 ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤቶችን በማፍረስ ነው የእድሳት ስራውን ያስጀመሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክረምቱ ወራት በየአካባቢያችን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ጎረቤቶቻችንን እንርዳ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ሁሉም ቢተባበር ችግሮቻችንን በአጭሩ መቅጨት እንችላለን ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ አቅም የሌላቸውን በምንችለው በመደገፍ መተጋገዝ ይኖርብናል ብለዋል።

(በአስታርቃቸው ወልዴ)