ጠ/ሚ ዐቢይ በአማራ ክልል አኩሪ አተርን ለማምረት ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገለጹ

ጥቅምት 7/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ በሚካሄደው ርብርብ አኩሪ አተርን ለማምረት ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ በክላስተር የለማ የአኩሪ አተር ማሳን ጎብኝተዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ38 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን የኩታ ገጠም ምርት ተመልከተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠገዴ ወረዳ አዲስ ዓለምም በኩታ ገጠም 1 ሺሕ 200 ሄክታር ላይ የተመረተውን አኩሪ አተር መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አመልክተዋል።

ያስገኙት ምርት በእጅጉ አበረታች ነው፤ በስንዴ አምራችነት ያገኘነውን አስደሳች ውጤት በሌሎች ምርቶችም እንደሚቀጥል ያመላክታል ብለዋል።

ሀገራችን የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣ በዓለም ገበያ በምርቶቿ መሳተፏ የሩቅ ጊዜ ህልም ሳይሆን፣ እየቀረበ የሚገኝ የጥረት ውጤት ነው ሲሉም አመልክተዋል።

በጉብኝት መርኃ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW