“ጥቁር አንበሳ” በሚል የተካሄደው የአየር ትርዒት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አለም አቀፍ የአየር ትርዒት ብራንድ ሆኖ ይቀጥላል – ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

የአየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

ታህሳስ 14/2016(አዲስ ዋልታ) 88ኛው የአየር ኃይል ቀን የበዓል አከባበር ላይ “ጥቁር አንበሳ” በሚል የተካሄደው የአየር ትርዒት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አለም አቀፍ የአየር ትርዒት ብራንድ ሆኖ እንደሚቀጥል የአየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።

88ኛው የአየር ኃይል ቀን የበዓል አከባበር በታላቅ ድምቀት መጠናቀቁን ተከትሎ ልዩ የምስጋናና የእውቅና ፕሮግራም ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ 88ኛው የምስረታ በዓል አከባበር በታሪካዊው የጥቁር አንበሳ የአለም አቀፍ የአየር ትርዒት እና በአፍሪካ የመጀመሪያው የአየር ኃይል ፎረምን ጨምሮ በሌሎችም ዝግጅቶች በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

ይህ ስኬት መላው የተቋሙ አባላት እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ በመስራታቸው የተገኘ ውጤት በመሆኑ ሁሉም ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

የቀረበው የአየር ትርዒት አለም የተደመመበትና አብራሪዎቻችንም በየትኛውም አለም አቀፍ የአየር ትርዒት ላይ መሳተፍ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው በተግባር ያረጋገጡበት ነበርም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“ጥቁር አንበሳ” የሚለው የአየር ትርዒት ከእንግዲህ ማንም መቀማት የማይችለውና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ብቻ የሆነ አለም አቀፍ የአየር ትርዒት ብራንድም ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

በዕለቱ ለአጋር ተቋማትና ድርጅቶች የተሻለ ውጤት ላሳዩ የስራ ክፍሎችና የጎላ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀትና ልዩ የገንዘብ ሽልማት ከአየር ኃይል አዛዥ እና ከጄኔራል መኮንኖች መበርከቱን ከሀገር መከላካያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡