ፈረንሳይ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደፍ ገለጸች

አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ

መጋቢት 17/2014 (ዋልታ) ፈረንሳይ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው ፈረንሳይ በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ሰብኣዊ ድጋፍ በማድረግ በተጨባጭ አጋርነት ማሳየቷን አውስተዋል።

አገራቸው ከዓለም ዐቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመሆን በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋር እና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሰብኣዊ ድጋፍ ፕሮጀክቶችን እየተገበረች ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ፈረንሳይ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም አገራቸው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን የደሴ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡

የፈረንሳይ መንግሥት በፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያ ስድስት ወራት 10 ሚሊዮን ዩሮ ለመልሶ ማቋቋምና ምግብ ዋስትና ፕሮጀክቶች የሚውል ገንዘብ መድቦ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምን ለማስፈን የወሰዳችው እርምጃዎችን እንደምታደንቅም ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ወርሃ ሰኔ ላይ መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ ሲወስን ፈረንሳይ ውሳኔውን በጽኑ መደገፏን አስታውሰው አሁንም አገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነች አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አይነተኛ ሚና እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በአፍሪካ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

125 ዓመታትን ያስቆጠረውን የኢትዮ-ፈረንሳይ ወዳጅነት በመዘከር በቀጣይ በበርካታ ጉዳዮች በጋራ እንሰራለንም ነው ያሉት፡፡

ሁለቱ አገራት በታዳሽ ኃይል በተለይም ደግሞ ጂኦተርማል፣ ሎጂስቲክስና በግብርናው መስክ  በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ ገልጸዋል፡፡

የፈረንሳይ ባለሙያዎች ቡድንን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ተቋርጦ የነበረውን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ዳግም ማስጀመር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር በሚከናወነው ሥራ ላይ ፈረንሳይ ተሳታፊ መሆኗንም አክለዋል፡፡

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!