ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – ለፋሲል ከነማ በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እስካሁን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቶለታል፡፡
“ስፖርት ለኢትዮጵያ” በሚል መርህ በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እስካሁን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ የዛሬው ቀን ፋሲል ከነማ ለኢትዮጵያ ኩራት የሆነበትና የአፍሪካዊያን ቀን ስለሆነ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች በርካታ ጀግኖች አሏት ያሉት አቶ ደመቀ፤ የዛሬው የገቢ ማሰባሰቢያም የፋሲል ከነማ ቡድንን ማገዝ ብቻ ሳይሆን ጀግኖች ኢትዮጵያንን ማገዝ ነው ። ፋሲል ከነማ መተባበርንና መተጋገዝን አስተምረውናል ።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ጎንደር ላይ ተሰባስበው ኢትዮጵያዊ ቡድን ሰርተው ምሳሌ ሆነዋል ይሄንን ኢትዮጵያዊ ቡድን ደግሞ ማገዝ ያስፈልጋል ። ለዚህም ነው ፋሲል ከነማ ከክለብም በላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“ፋሲል ከነማ በተለያዩ ችግሮች አልፎ ከዚህ መገኘቱ የሚያኮራ ነገር ነው ነገር ግን በርካታ ችግሮች አሉበት። እነዚህን ችግሮች ደግሞ በመንግስትና በተለያዩ ተቋማት ትብብር መቀረፍ አለባቸው።
ፋሲል ከነማ በአፍሪካና በተለያዩ መድረኮች ደምቆና አኩሪ ታሪክ እንዲያስመዘግብ የክልላችን መንግስት ከጎኑ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር ናቸው።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩ ላይ ክልሎች፣ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶች እና ግለስቦች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ቃል እየገቡ ሲሆን እስካሁን ድረስ በድምሩ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቷል።
(ምንጭ፡- ኢፕድ)