ደቡብ ሱዳን ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች

አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን

ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – ደቡብ ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ገለጹ።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካላት ትልቅ ሚና አኳያ የውስጧን ሰላም በማስጠበቅ የቀጣናውን ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ልትመራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን የናይል ውኃ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት በመሆኑ ሁሉም ያለምንም ችግር ሊጠቀምበት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በውኃው ላይ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ልማታዊ ጎናቸው መታየት አለበት ያሉት አምባሳደሩ፣ ችግሮች ካሉም ሀገራቱ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦችም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሦስቱ አገራት ወደ ዘላቂ መፍትሄ መምጣት እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።

የአፍሪካ ኅብረት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ቁመና እያለው ለመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ ለሌላ አካል ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ አያስፈልግም ብለዋል።

አፍሪካ ኅብረትም የታዛቢነት ሚና ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ሥልጣን እንዳለው በመረዳት ሁነኛ መፍትሄ ለመሥጠት መሥራት እንደሚገባው የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ኅብረቱ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህም እውን ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በሌላ በኩል “ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ሠላም አዋላጅ ነች” ያሉት አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሠላም ግንባታ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰላፊ ሀገር ናት እንደሆነችም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ተስፋ ሳትቆርጥ ሀገራቸው አሁን ላለችበት ሰላምና መረጋጋት እንድትደርስ አበርክቶዋ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የአየር፣ የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የመክፈትና የማጠናከር ሥራ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ይህንንም በተመለከተ ከሚመለከተው ከኢትዮጵያ ተቋምና ከከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ የመግባቢያ ሥምምነት ሠነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በአከበቢው ካላት ሚና አኳያ ውስጣዊ ሰላሟን በማስጠበቅ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በቀዳሚነት ልትመራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ቀጣናው የሚከተለው ነጻ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በምጣኔ ሃብት ማስተሳሰር ከቻለች የቀጣናው አገራት ወደ ልማትና እድገት የመምራት እድሏ ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ከገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት አገግማ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰላሟ እየተመለሰች ትገኛለች።