ፌደራል ፖሊስ ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

ፌደራል ፖሊስ

ግንቦት 24/2015 (ዋልታ) ሆን ብለው ኅብረተሰቡን ለማሳሳት ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ተቋሙ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀምበት የነበረውን ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራን መዝጋት ነው ያለው ፌደራል ፖሊስ ይሄንን ተከትሎ በፖሊስ የወንጀል ምርመራ ስራ ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስር ነቀል ማሻሻያ ማድረጉን አስታውሷል፡፡

ከሪፎርሙ በኋላ ተቋሙ የወንጀል ምርመራ አሠራሩን በመቀየር በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልፅ አሰራር በመዘርጋት ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወንጀል ምርመራ ስታንዳርድን እየተከተለ ይገኛል ብሏል። በዚህም ውጤታማ የወንጀል ምርመራ ሥራ በመስራት የተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብት አያያዝ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል ችሏል ሲል ለዋልታ በላከው መግለጫ አመልክቷል። በዚህ ተግባሩ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት የምስጋና እና የእውቅና የምስክር ወረቀት መሰጠቱ ይታወቃል ሲልም አክሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በተጠርጣሪዎች ላይ ኢሰብአዊ አያያዝ ፈጽሟል እያሉ ሆን ብለው የተቋሙን መልካም ስም ለማጠልሸት ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ይህንን መሠረተ ቢስ ውንጀላ እየፈፀሙ ያሉት በአሸባሪነት ተጠርጥረው እንደሚፈለጉ ስም ዝርዝራቸው ለህዝብ በይፋ ከተገለጹት መካከል መሆናቸው ተደርሶባቸዋልም ነው ያለው የፌደራል ፖሊስ በመግለጫው።

ይህንን ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ያዋሉ ግለሰቦች ላይ እያካሄደ ያለውን የምርመራ ሂደት ለማደናቀፍ እንደሆነም ታውቋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአሸባሪዎች ላይ የጀመረውን የምርመራ ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ኅብረተሰቡ በዚህ ሐሰተኛ ወሬ ሳይደናገር ትክክለኛው መረጃ በቦታው ተገኝቶ ከፖሊስ እና ከተጠርጣሪዎች አንደበት ማረጋገጥ እንደሚችል አስታውቋል።