ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ ለትርፍ ያልተቋቋመ ትምህርት ቤት ሆኖ እንዲቀጥል ከስምምነት ተደርሷል፡፡
በዛሬው እለት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት አመራሮችን አነጋግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ቀድሞ ከተቋቋመለት አላማ ጋር አለመጣጣም በመታየቱ ምክንያት ከተማሪ ወላጆች እና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የትምህርት ቤቱን እጣ ፈንታ ለመወሰን የትምህርት ሚኒስቴር ከግሪክ አምባሳደር፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከግሪክ ማኅበረሰብ አባላት ተወካዮች፣ ከግሪክ ትምህርት ቤት አመራሮች እና ከተማሪ ወላጆች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በተደረገው ውይይትም ትምህርት ቤቱ የግል ትምህርት ቤትነትን እና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤትነትን ባህሪ አጣምሮ በመያዝ መቀጠል እንደማይችል በማሳወቅ አንዱን መርጦ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ተደርጓል፡፡
በዚህም መሰረት በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ትምህርት ቤቱ ከግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤትነት ለትርፍ ወደ አልተቋቋመ ትምህርት ቤትነት ለመቀየር ከውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡
ትምህርት ቤቱም እስከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ድረስ አግባብ ባለው አካል ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን ኦዲት በማድረግ የኦዲት ሪፖርት እንዲያቀርብ፣ አደረጃጀቱን በሚመለከት ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ ባወጣው መመሪያ መሰረት እንዲተገብር ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡