በምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች በአቮካዶ ምርት ውጤታማ እየሆኑ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ)   በምስራቅ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች አቮካዶ በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑ ተገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል የልማት ኢንሼቲቭ ተቀርጾላቸው አርሶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ እያደረጉ ከሚገኙ ምርቶች መካከል ሙዝ፣ አቮካዶና ፓፓዬ ተጠቃሽ ናቸው።

በተለይም አቮካዶን ጥራት ባለው ሁኔታ በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ አርሶ አደሮቹን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ምስራቅ ወለጋም ለተሻሻለው የአቮካዶ ምርት ምቹ ስነ-ምህዳር ያለው በመሆኑ ባለፉት አመታት ለአርሶ አደሩ በተሰራጨ ችግኝ ውጤታማ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

በዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት የቡና እና ፍራፍሬ ስራ ቡድን መሪ አሰፋ መኮንን እንደገለጹት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የተዳቀሉ የአቮካዶ ችግኞች ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ መተከሉን ገልጸዋል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ በተደረገላቸው ድጋፍና ክትትልም ምርቱ ደርሶ አርሶ አደሩ፣ የአካባቢው ህብረተሰብ መጠቀም መቻላቸውን ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በተሰራ ስራ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ተናግረው፤ በሰባት የተለያዩ ወረዳዎች ለሙከራ የተጀመረው ስራ አሁን ላይ በስፋት በሁሉም ወረዳዎች በመልማት ላይ ነው ብለዋል።

በኩታ ገጠም ዘዴ እየተሰራ የሚገኘው የአቮካዶ ልማት ለአካባቢው ገበያ ከመቅረብ አልፎ ምስራቅ ሸዋ በሚገኘው በሉሜ የአቮካዶ ምርት ላኪ ድርጅት በኩል ወደ ውጪ ገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም 3 ሺሕ 500 የሚደርሱ ነዋሪዎች በቀጥታ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ 1 ሺሕ 279 ሄክታር መሬት በአቮካዶ ምርት የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም በየአመቱ በአካባቢው ገበያ ከሚሸጠው ውጪ 600 ኩንታል ለውጭ ገበያ መቅረብ ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ2015/16 የምርት ዘመንም በዞኑ 120 ሺሕ ተጨማሪ የተሻለ ዘር ያለው የአቮካዶ ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።