ኢትዮጵያን በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚወክሉ አትሌቶች ሽኝት ተደረገላቸው

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ)  ከነሐሴ 13 እስከ 21 ቀን 2015 በሀንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ በሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ኢትዮጵያን በመወከል የሚወዳደሩ አትሌቶች ዛሬ ሽኝት ተደረገላቸው።

በዚህ ሻምፒዮና ከ200 ሀገራት የተውጣጡ 2 ሺህ ያህል አትሌቶች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በሚጀመረው በዚህ ውድድር ኢትዮጵያም ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉ የውድድር ርቀቶች እንደምትወዳደር ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያም በዚህ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ19 ሴት እና በ16 ወንድ በድምሩ በ35 አትሌቶች ትወከላለች።

በሽኝት መርሃ-ግብሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ቀጀላ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።