ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ወታደራዊ አታሼዎች የህዳሴ ግድብን ጎበኙ

ጥቅምት 30/2016 (አዲስ ዋልታ) ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ።

በጉብኝቱ የኢፌዴሪ መከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ፣ የ47 አገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ በዚህ ወቅት፤ የህዳሴ ግድብ ቀጣናውን በልማት የሚያስተሳስር ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጉብኝቱ ዓላማም ወታደራዊ አታሼዎች ግድቡ ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር ያለውን ፋይዳ እንዲሁም በታችኛው የተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱና እውነታውን እንዲረዱ ማድረግ መሆኑን መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ገፅ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ግድቡ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ እውቀትና ላብ እየተገነባ የሚገኝ አዲስ ብሔራዊ ኩራት መሆኑንም ጠቅሰዋል።