በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል አስፈጻሚ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ, መስከረም 30 ቀን 2004 (ዋኢማ) – በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል አስፈጻሚ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የኢፌዲሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።

ተቋሙ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የካቢኔ አባላት ጋር በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የአንድ ቀን አውደ ጥናት አካሂደዋል።

በዚህ ወቅት የኢፌዲሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ሠራዊት ስለሺ እንደገለጹት በአገሪቱ የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እንዳይደናቀፍ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ሚና የጎላ ነው።

በተለይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታየውን አገራዊ ንቅናቄ ለማስቀጠል የመልካም አስተዳደር መስፈን ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል።

እንዲሁም የመልካም አስተዳደር መስፈን በአገሪቱ እየተገነባ ላለው የዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከርና የአምስት ዓመቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአገሪቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት በመልካም አስተዳደርም ለመድገም ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የመልካም አስተዳደር መስፈን ለዜጎች ህልውና አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑ የሚታመንበት መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂዋ እስከ አሁን በመስኩ የተመዘገቡ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም ብዙ ርቀት ለመጓዝ ግን በርካታ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ ሠራዊት ማብራሪያ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ምክክር ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት በየክልሉ የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን ለማስቀረት፣ የችግሮቹን መንስዔ ለማወቅና የመፍትሔ ሀሳብ ለመሻት ነው።

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ሺህ 457 የአስተዳደራዊ በደል አቤቱታዎችን ተቀብሎ ምርመራ በማድረግ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል።

በአስራ ሦስት ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራ በማካሄድ የታዩ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳብ ያመላከተ ሲሆን ችግሮቹ በአፋጣኝ እንዲፈቱም ከተቋማቱ አመራር አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱንም አስረድተዋል።

በፌዴራልና በክልል ተቋማት የቅሬታ ሰሚን በማደራጀት በኩል እየተወሰደ ያለው አዎንታዊ እርምጃ በዕንባ ጠባቂ ተቋም ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ ከመቀነሱም በላይ የዜጎች የጊዜ፣ የገንዘብና የጉልበት ብክነት በአንጻራዊ መልኩ ቀነሷል ብለዋል።

የተቋሙን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን መክፈቱን ጠቁመዋል።

የኢፌዲሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከ1999 ዓ/ም እስከ 2003 ዓ/ም ድረስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2 ሺህ 533 የአስተዳደራዊ በደል አቤቱታዎችን ሲቀበል ከኦሮሚያ ክልል 1 ሺህ 162፣ ከአማራ ክልል ደግሞ 422 አቤቱታዎችን ተቀብሏል።

ለተቋሙ ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል ከአሰሪና ሠራተኛ ጋር በተያያዘ 1 ሺህ 487 አቤቱታዎች፣ ከንብረት ጋር የተያያዙ ደግሞ 1 ሺህ 378 ይጠቀሳሉ።

ተቋሙ ለአንድ ቀን ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ የኢፌዲሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ስልጣንና ተግባር፣ የአስተዳደር ፍትህና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የመረጃ ነፃነት አዋጅ ክፍል ሦስት ድንጋጌዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት መደረጉን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።