ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የሽግግር መንግስት መጠናከር የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች-ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2004 (ዋኢማ) –  ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የሽግግር መንግስት መጠናከር የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር አብዱልወሊ መሀመድ ዓሊን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደገለጹት የሶማሊያ የሽግግር መንግስትን ለማጠናከር ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ለመቀጠል ዝግጁ ናት።

በተለይ የሽግግር መንግስቱን ለማጠናከር በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት /ኢጋድ/ የተነደፈውን ብሔራዊ የደህንነትና መረጋጋት ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

እንዲሁም በሶማሊያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለረሀብ የተጋለጡ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ዕርዳታና ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደምትገኝም አስረድተዋል።

በቅርቡ አልሸባብ በሶማሊያ ንጹሐን ዜጎች ላይ ባደረሰው ጥቃትም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በኢትዮጵያ ሕዝብና በራሷቸው ስም ገልጸዋል።

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር አብዱልወሊ መሀመድ ዓሊ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የጋራ ስትራቴጂ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።

አልሸባብ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና የሶማሊያን የሽግግር መንግስት ለማጠናከር በተነደፈው የጋራ ስትራቴጂ ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያና የሶማሊያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይም ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን የኢዜአን ጠቅሶ ዋኢማ ዘግቧል።