የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት አዋጆችን አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2004 (ዋኢማ) -ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋምና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ እንደገና ለመደንገግ የወጡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ።

የምክር ቤቱ ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባን ትናንት ሲያካሂድ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ ያስፈለገው በሚቀጥሉት ዓመታት በመንግስት የታቀዱ ሰፋፊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት መስኮችን እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር በመዘርጋት ተደራሽነትን በማስፋት ኮሚሽኑ የጀመረውን የአሰራር ለውጥ ሥርዓት ከግብ ለማድረስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበሩ እና ከሌሎች መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ወደ ኮሚሽኑ የመጡ ሥራዎችን አሰባስቦ በግልጽ በኮሚሽኑ ስልጣንና ኃላፊነት እንዲካተቱ ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል። ከህብረተሰቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጥምረት በመስራት የወንጀል ሥጋቶችን በመከላከል የአገሪቱን ፈጣን የልማት እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጁ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በአንድ ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።  በሌላ መልኩ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ እንደገና ለመደንገግ ያስፈለገበት ምክንያት መንግስት በከተማ መሬት ላይ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነትን በመናድ በምትኩ የልማታዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚን ለመፍጠር እና ለማጠናከር መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ከአገሪቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር አቅጣጫዎች አንፃር ግልጽና ተጠያቂት የሰፈነበት አሰራር እና የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል። የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ እንደገና ለመደንገግ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይት በማድረግ በአንድ ድምፀ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቃቸውን የኢዜአ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።