በውጭ ጉዳይ ዋና መስሪያ ቤቶትና በኢምባሲዎች ሲካሄድ የነበረው የሰው ኃይል ምደባ በሚቀጥለው ሳምንት ይጠናቀቃል

በዋና መስሪያ ቤትና በኢምባሲዎች የተጀመረው የሰው ኃይል ምደባ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጠናቀቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አዲሱን መዋቅራዊ አደረጃጀት ተከትሎ የሰው ኃይል ምደባ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ የ31 ከፍተኛ አመራሮች ምደባ ያደረገ ሲሆን፥ በአዲስ ምደባ ውስጥ ከተካተቱት  አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ወጣቶች እንደሆኑ ተገልጿል።

መዋቅራዊ ለውጡ አምስት ቋሚ ተጠሪ አደረጃጀቶች እንዲኖሩ ተደርጓል ፥እስከ 25 ዓመት ልምድ ያላቸው አምባሳደሮች እንደተመደቡ ተጠቁሟል።

የአምስቱ ተጠሪ አደረጃጀቶች ኃላፊነትም የመስሪያ ቤቱን  የዕለት ከዕለት ስራ ማቀላጠፍ  እንደሆነና የሚኒስትሩና ሚነስትር ደኤታዎች ዋና ትኩረት ፓሊስና ስትራቴጂ ላይ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እየተካሄደ የሰው ኃይል ምደባው የተለያዩ  መስፈርቶችን  መሠረት ያደረገ እንደሆነም  ተገልጿል ።

በዚህም በፓለቲካዊ አመለካከት ብቻ ሳይሆን በሙያን መስፈርት  ፣ተቋሙ እያካሄደ ያለውን የፓሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን  የማድረግ አቅም ያላቸው  ናቸው ተብሏል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ምደባው  የተሳለጠ ለማድረግ የአምባሳደሮች ጥሪና ሹመት እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ተናግረዋል ።