የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

በ250 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻልና የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት የምንገኝበት ወቅት አለም በቴክኖሎጂ አንድ የሆነበት በመሆኑ በከተማችንም ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ ቴክኖሎጂን በማበልጸግ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአገልግሎት መስጫ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ተግባራዊ መሆን አገልግሎት ፈላጊውን አካል የጊዜ፣ የጉልበትና እንግልት እንደሚቀንስ ጠቅሰው ብልሹ አሰራሮችን ለመከታተል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የህብረተሰቡን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ዛሬ የተተገበሩ መሰል የዲጂታል የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን በብዛት ማስፋፋት እንደሚገባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን አህመድ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የዲጂታል መሠረተ ልማት ዝርጋታ አበረታች በመሆኑን  ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የወረፋ ማስጠበቂያ ሲስተም፣ ከተማ አቀፍ የሜይል ሲስተምና ሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችንም ስራ አስጀምረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ አማካኝነት በ250 ሚሊዮን ብር ወጪ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የህብረተሰቡን አገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻል የሚያስችሉ የኢ-ሰርቪስ መሰረተ ልማት ዝርታዎችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ከበአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪያት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡