አሜሪካ በአዲሱ አይነት የኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ማግኘቷን አስታወቀች

በእንግሊዝ የተገኘውና በፈጣን ሁኔታ የሚተላለፈው አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት መገኘቱን አሜሪካ ይፋ አድርጋለች።

አዲስ ባህሪ ያለው ኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘው ምንም የቅርብ የጉዞ ታሪክ በሌለው የ20 ዓመት ግለሰብ ላይ ሲሆን ግለሰቡ በለይቶ ማቆያ መግባቱም ተገልጿል።

የግዛቱ የጤና ባለስልጣናት ከግለሰቡ ጋር ግኑኝነት ያላቸውን ሰዎች እና አዲስ ባህሪይ ካለው ቫይረስ ጋር ንክኪ ያላቸውን ለመለየት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

አዲስ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የኮቪድ-19 ክትባት ስርጭት ከታሰበው መረሃ ግብር ወደኃላ በመቅረቱ ክትባቱን ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው እንቅስቃሴ እንደሀገር ከባድ ፈተና ውስጥ ገብተናል ሲሉ የዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር ወቅሰዋል።

በአሜሪካ ከ19 ሚሊየን በላይ ሰዎች በኮቪድ- 19 የተያዙ ሲሆን ከ337 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

አዲስ ተገኘ የተባለው የኮቪድ-19 ስርጭቱ ከቀድሞው ቫይረስ በባህሪው ፈጣን ሲሆን በበሽታው የተጠቁት ላይ ግን የተለየ ባህሪ እንደሌለው የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

አዲስ ባህሪ ያለው ቫይረሱ በአሜርካ እንደታየው ሁሉ በካናዳ እና በተለያዩ ሀገራትም እየተገኘ ሲሆን የመጀመሪያውን እና ሁለተኛውን የኮቪድ-19 ባገናዘበ መልኩ ክትባቱ በአሜሪካ እየተሰጠ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የአሜሪካ መንግስት እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ 20 ሚሊየን ዜጎቹ የኮቪድ-19 ክትባት ሊሰጥ የታቀደ ሲሆን አስካሁን 2.1 ሚሊየን ሰዎች ክትባት መውሰዳቸውን የሀገሪቱ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል አስታውቋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የቀረበው አስትራዜኒክ የተባለውን የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለመስጠት እንግሊዝ ውሳኔ ላይ መድረሱዋንም አስታውቃለች።

እንግሊዝ አስትራዜኒክ የተባለውን ክትባት ፋብሪካዎች በ100 ሚሊየን ዶዝ እንዲያመረቱ ያዘዘች ሲሆን የብዙዎችን የመከላከል አቅም በማሳደግ ወደ ቀደመ ጤንነታቸው እንዲመለሱ ያስችላልም ተብሏል።