በጋምቤላ ከተማ ሆስፒታሎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረጉት ጥረት የሚበረታታ ነው – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

በጋምቤላ ከተማ አጠቃላይና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ለህብረተሰቡ የተሻለ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ከቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬና የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር  ዛሬ ሆስፒታሎቹን ተመልክተዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት በዚህ ወቅት ሆስፒታሎችን በመሰረተ ልማት በማደራጀትና የተለያዩ የጥራት ማረጋገጫ ስራዎችን በማከናወን ለህፃናት፣ እናቶችና ሌሎች ታካሚዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው።

ቀደም ሲል ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ እንደ ሌሎች አካባቢዎች በሆስፒታሎች ተቀዛቅዞ የነበረው የመደበኛ የህክምና አገልግሎት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ሆስፒታሎች ከመደበኛው የህክምና አገልግሎት በተጨማሪ የኮሮናቫይረስን በመከላከልና በማከም ረገድም እንዲሁ ሰፊ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ቢሆንም ጋምቤላን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህንን ችግር ለማቃለል የተጠናከረ የንቅናቄ ስራ በቅርቡ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በሆስፒታሎች የሚጠበቀውን መሰረታዊ አገልግሎት ለማሟላት የሚደረጉት ጥረቶች መልካም መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በክልሉ ከፍተኛ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት እንደነበረ ጠቁመው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ስራዎች የስርጭቱ መጠን የመቀነስ አዝማሚያ እንዳሳየ መገንዝብ እንደቻሉም  ገልጸዋል።

በሆስፒታሎቹ ምልከታ ያደረጉት ያሉትን ክፍተቶች በመለየት ፋውንዴሽናቸው የተለያዩ እገዛዎችን ለማድረግ በማሰብ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሯና የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት በጋምቤላ እስከ ነገ በሚኖራቸው ቆይታ በኮሮናቫይረስ መከላከል፣ በጨቅላ ህጻናት የጤናና የስርዓተ ምግብ ዙሪያ ከዘርፉ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ኢዜአ ዘግቧል።