የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫን ለማከናወን ሕጋዊ ምዝገባ ላጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥር 13-18 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት የምርጫ ምልክት እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርቧል።
ቦርዱ ባወጣው መረጃ መሠረት የምርጫ ምልክት መረጣው እንደሚከተለው የሚከናወን መሆኑንም አመልክቷል።
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ምልክትነት ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ምልክቶችን ያዘጋጀ ሲሆን የፓርቲ ተወካዮች ከተዘጋጁት ምልክቶች ሊወክለኝ ይችላል የሚሉትን ይመርጣሉ።
- የመረጡት ምልክት በፓርቲያቸው የተያዘ መሆኑን ያስመዘግባሉ።
አንድ ፓርቲ ያስመዘገበው ምልክት ከሚመረጡ ምልክቶች ዝርዝር ውስጥ ይወጣል።
- በቦርዱ ከተዘጋጀው ምልክት ውስጥ የሚፈልጉትን ምልክት ያላገኙ ወይም የራሳቸውን ምልክት ማስመዝገብ የሚፈልጉ ፓርቲዎች የሚከተሉትን ነገሮች ማሟላት አለባቸው።
– ምልክታቸውን አትመው ለማስመዝገብ ይዘው መምጣት አለባቸው።
– የምልክታቸውን ዲጂታል ፎርማት በፍላሽ ማቅረብ አለባቸው።
– ምልክታቸው በጥቁር እና ነጭ ቀለም የተዘጋጀ መሆን አለበት።
– ምልክታቸው 2 ሲሜ በ2 ሴሜ መሆን አለበት
– የጥራት መጠኑ 200-300 ፒክስል መሆን አለበት
– የፋይሉ መጠን ቢበዛ 200 ኪሎባይት መብለጥ የለበትም
- የምርጫ ምልክት መረጣው የሚከናወነው ከጥር 13- 18 ሲሆን ቦርዱ ከ18-24 ባለው ጊዜ ውስጥ የማጣራት እና የመወሰን ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል።
- ከጥር 13-18 ቀን 2013 በሚደረገው የምልክት መረጣ ላይ ማንኛውም ሕጋዊ ምዝገባቸውን ያጠናቀቁ ፓርቲዎች በሥራ ሰዓት ቦሌ ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት ባለው የሺ ሕንፃ 7ኛ ፎቅ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ማእከል ይከናወናል ብሏል ቦርዱ።
- ይህ የምርጫ ምልክት መረጣ የግል እጩዎችን የማያካትት ሲሆን፣ የግል እጩዎች ምልክታቸው የሚመርጡበት መንገድ ወደፊት በቦርዱ የሚገለጽ መሆኑንም ቦርዱ ገልጿል።