የካቲት 24/2013 (ዋልታ) – በሰው የመነገድ እና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የችግሩ ምንጭ በሆኑ ህገወጥ ደላሎች ላይ መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ዜጎች በጥቂት ደላሎች እና ህገወጦች ተታለው በሰው ሀገር መሰቃየታቸው ቅስም ሰባሪ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፣ በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት በሳውዲ አረብያ ብቻ ከ34 ሺህ በላይ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
በህገወጥ መንገድ ሳውዲ አረቢያ ገብተው የሚሰቃዩ ወገኖችንን ለመታደግ መንግስት በሳምንት 1ሺህ ስደተኞችን ወደ አገር ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሆኖም ችግሩ መቀረፍ የማይችል በመሆኑ ህገወጥ ደላሎችን በመቆጣጠር የችግሩን ምንጭ ከስሩ ማድረቅ እንደሚገባ እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በህገወጥ መንገድ ሲጓዙ ህይወታቸውን ከማጣታቸው ባሻገር ለአካል ስርቆት፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለወሲብ ጥቃት ተጋልጠዋል ብለዋል።
በዚህም ዋና ተዋንያኑ በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገርን ወንጀል የሚሰሩ ደላሎች በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ ንቅናቄው አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል።
ዜጎች በህጋዊ መንገድ በውጭ ሀገር መስራት እንዲችሉ፣ በአገር ሰርቶ መለወጥ ትኩረት እንዲሰጠው ብሎም በህገወጥ መንገድ ድንበር የሚያሻግሩ ደላሎችን ለመቆጣጠር ሁሉም ሀላፊነት ስላለበት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
በሰው መነገድ እና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ሂደት ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል ያሉት የአለም ስራ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አሌክሲዮ ሙሲንዳ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችው የንቅናቄ መድረክ የሚበረታታ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
በዚህ የንቅናቄ መድረክ ላይ በሰው የመነገድ እና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ላይ የሚያጠነጥኑ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ከሚመለከታቸው አካላት ውይይት ተደርጎባቸው የማጠቃለያ የስራ መመሪያ ይሰጥባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
(በቁምነገር አህመድ)