በጂቡቲ ጀልባ ላይ ባጋጠመ አደጋ ቢያንስ 34 ስደተኞች መሞታቸው ተገለጸ

በጂቡቲ ጀልባ ላይ ባጋጠመ አደጋ

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – ቢያንስ 34 የሚሆኑ ስደተኞች በጂቡቲ የባህር ዳርቻ ሰጥመው መሞታቸውን አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት፣ አይኦኤም አስታውቋል።

ስደተኞቹ መነሻቸውን ያደረጉት በጦርነት ከምትናጠው የመን እንደሆነና በጀልባዋ ላይም 60 ስደተኞች ተሳፍረው እንደነበር ተገልጿል።

ጀልባዋ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የተሳፈሩባት እንደሆነ አይ ኦ ኤም አስታውቋል።

ጀልባዋ በማጋደሏ ስደተኞቹ መስጠማቸው የተነገረ ሲሆን፣ ለጀልባዋ ማጋደል የተገለፀ ምክንያት የለም።

መነሻቸውን ከአፍሪካ ቀንድ ያደረጉ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አደገኛና አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ የሚደረገውን ጉዞ አቆራርጠው ለተሻለ ህይወት ወደ ገልፍ አገራት ያቀናሉ።

ይህም ሁኔታ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አይ ኦ ኤም አስታውቋል።

በባለፈው ወር ቢያንስ 20 የሚሆኑ አፍሪካውያን ስደተኞች በጅቡቲ ባህር ዳርቻ አካባቢ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከጀልባ ላይ ተወርውረው ሕይወታቸው ማለፉን የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል።

የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በበኩሉ፣ አዘዋዋሪዎቹ ጀልባው ከሚገባው በላይ መሙላቱን ሲያስተውሉ “ቢያንስ 80 የሚሆኑትን ስደተኞች ወደ ውሃ ገፍትረዋቸዋል” ብሏል።

ጀልባው 200 የሚሆኑ ስደተኞችን ጭኖ የነበረ ሲሆን፣ ከስደተኞቹ መካከልም ሴቶችና ህጻናት ይገኙ እንደነበር የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።

አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ የመን ጉዟቸውን እያደረጉ የነበረ ሲሆን፣ ከየመን ደግሞ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በማቅናት የተሻለ ህይወትና ስራ ለማግኝት የሚሞክሩ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።