ሙስሊሙ ህብረተሰብ የረመዳን ፆምን በፍቅርና በመተጋገዝ እንዲያሳልፍ ተጠየቀ

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – ሙስሊሙ ህብረተሰብ የ1442ኛውን የረመዳን ፆም ለፈጣሪው በመገዛት፣ በፍቅር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊያሳልፈው እንደሚገባ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለህዝበ ሙስሊሞች ዛሬ የተጀመረውን የ1442ኛውን የረመዳን ፆም በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሊ መሃመድ ሽፋ የረመዳን ፆም መጀመርን አስመልክተው፤ ረመዳን ወር የእዝነት፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የተቀደሰ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀው፣ ችግረኞችን፣ አቅመ ደካሞችን እንዲሁም ወላጅ አልባ ህጻናትን በማገዝና ምጽዋት በመለገስ ህዝበ ሙስሊሙ እንዲያሳልፍ ጥሪ አስተላልፈዋል::
ረመዳን የእዝነትና የራህመት ወር በመሆኑ በከተማው የሚገኘው ሙስሊሙ ህብረተሰብ የረመዳን ወርን በኢባዳ፣ በፍቅር፣ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ሊያሳልፈው እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የፅኑ ህሙማን ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱን አስታውሰው፣ በዚህ በተቀደሰ ወር ውስጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለፀሎት በሚሰባሰብበት ጊዜ የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፏቸውን ምክሮች በመቀበልና በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል::
እንደ ኢፕድ ዘገባ በተለያዩ ክልሎች የሚታዩ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፤ የመፈናቀል፣ ለንብረት መውደም እንዲሁም ለህጻናት፣ ለእናቶችና አዛውንቶች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን አስታውሰው፤ የእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮትና የእምነቱ መሪዎች አጥብቀው እንደሚያወግዙም ተናግረዋል::
ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን በማውገዝ ለህዝቡ መልካም በማሰብና ቅድሚያ በመስጠት ችግሩን በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል::
የህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከውጭ ኃይሎች እየተቃጣ ያለውን ትንኮሳ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በአገራዊ መንፈስ በመቆም ሊያወግዙት እንደሚገባ ገልጸው፣ ለጋራ ሀብታቸው በጋራ በመቆም ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች እገዛ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መክረዋል::