መከላከያ ሚኒስቴር የፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ ሂደቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ ሂደቱን አጠናክሮ መቀጠሉን የምድር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ገለፁ፡፡

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመሰረታዊ ውትድርና ሙያ ያሰለጠናቸውን 2ኛ ዙር ምልምል ወታደሮች አስመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የእለቱ የክብር እንግዳና የምድር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌ/ጄነራል አስራት ዴኔሮ ፣ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ተቋማዊ ግቦች መካከል አንዱ የፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ መሆኑን ጠቁመው ፣ በዚህም መሰረት ተቋሙ በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ሙያዊ ብቃቱ የተረጋገጠ ሰራዊት እየገነባ ይገኛል ብለዋል።

ተመራቂዎች ወደ ግዳጅ በሚሰማሩበት ወቅት ሃገርና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ ፣ ተመራቂዎች በቆይታቸው የስነ ልቦና ግንባታ ፣ የአካል ብቃት ፣ የተኩስ ፣ የስልትና ልዩ ልዩ ትምህርቶችን በተግባርና በንድፈ ሃሳብ መውሰዳቸውንና በተቋሙ ከተቀመጠው ግብ አንፃርም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን አረጋግጠዋል ።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ አህመድ መሃመድ በሰጡት አስተያየት ፣ ተመራቂዎች በሰሜን ዕዝ የተቃጣበትን የክህደት ተግባር ቀልብሶ በአጭር ጊዜ የጁንታውን ሃይል የደመሰሰ ሃይል አካል በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል። በቀጣይም ለሃገራችሁ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንደምታደርጉ እምነቴ ነው ሲሉ አክለዋል።

ከተመራቂ ወታደሮች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ፣ በቆይታቸው የቀሰሙትን ወታደራዊ ሳይንስ ወደ ተግባር በመቀየር ጁንታውን ጨምሮ ሌሎች ለሃገራችን ሰላምና ደህንነት ጠንቅ የሆኑ አካላትን ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በስልጠና ወቅት ያዳበሩትን ወታደራዊ እውቀትና ክህሎት ለዕለቱ የክብር እንግዶች ማሳየታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡