ሚያዚያ 02/ 2013 (ዋልታ) – በኢንቨስተርነት ስም የማጭበርበር ወንጀል የሚፈጽሙ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዳሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ እንዳረጋገጠው፤ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች ‘ኢንቨስተር ነን’ በሚል በሚፈጽሙት የማጭበርበር ወንጀል በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሀብትና ንብረት ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ማንነት በጥናት በመለየትና ቀረቤታ በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ወንጀል እየፈፀሙባቸው መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን አመልክቷል።
እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ለኢንቨስትመንት የመጡ በማስመሰል፣ አብረዋቸው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን እንደሚፈልጉ በማግባባትና ለስራ ማስኬጃም ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዳላቸው በመግለጽ ኢትዮጵያዊያንን ካገኙ አብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ በማስመሰል የሚያጭበረብሩ መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ አሳውቋል፡፡
እነዚህ አጭበርባሪዎች የኛ ዜጎች አብረዋቸው ቢሰሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳመን እና ከዚህ በተጨማሪም ዶላር የማባዛት ችሎታ እንዳላቸው በመግለፅ በተግባር አባዝቶ ለማሳየት እንደሚሞክሩም ገልጿል።
“መጀመሪያ የያዙትን ዶላር ሌላ ቦታ በፖስታ በመደበቅና ይባዛበታል ያሉትን ወረቀት ኬሚካል ውስጥ በመንከር ከዚያም የተነከረውን ወረቀት አውጥተው እንዲደርቅ በማድረግ በሌላ ፖስታ ውስጥ ያስቀመጡትን ትክክለኛ ዶላር በእጥፍ እንዳባዙት በማስመሰል ለሰዎቹ ያሳዩና ይበልጥ አመኔታን ለማግኘት ተባዛ ያሉትን ዶላር ባንክ ቤት ይዘው እንዲሄዱና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲመጡ ካደረጉ በኋላ አሁን የተባዛውን ዶላር ትክክለኛ መሆኑን ስላረጋገጥን እስከ አንድ ሚሊየን ዶላር ይዛችሁ ኑና እናባዛ በማለት ወደ ማጭበርበር ተግባር እንደሚያስገቡ ታውቋል” ብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የብር ኖትም በእጥፍ ማባዛት እንደሚችሉ በማስረዳትና ሃብታም እንደሚሆኑ በማሳመን ዜጎች ያላቸውን ገንዘብ ይዘውላቸው ሲሄዱ ግማሾቹ ከነገንዘቡ ታፍነው ግማሾቹ ደግሞ ራሳቸውን ስተው እንደተገኙና ገንዘባቸውንም እንደተቀሙ ማረጋገጥ እንደተቻለ ፖሊስ አመልክቷል።
የዚህ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባዎችም ቤተሰቦቻቸው መበተኑን፣ ለድህነትና ለጤና መታወክ መዳረጋቸውን ማረጋገጡን የገለፀው ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ፤ ህብረተሰቡ ሁኔታውን ተገንዝቦ የማይገባ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ለአጭበርባሪዎች ሲሳይ እንዳይሆን አሳስቧል።
ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥመው በቅርብ ላሉ የፀጥታ አካላት ወይንም በነፃ የስልክ መስመር 987 በመደወል ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ አስታውቋል።