የዕለት ደራሽ ድጋፍን ከማሳለጥ በተጨማሪ በየአካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋምና መሠረተ ልማትን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገው ርብርብ መቀጠሉን የብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስታወቀ።
የሚኒስትሮች ኮሚቴው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻ ተከትሎ በአካበቢው ለተከሰቱ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ የማቋቋም ሂደት በትኩረት እንደሚገኝ ሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኮሚቴው በየጊዜው አስቸኳይ ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ በመለየት፣ አፈጻጸማቸውን በመከታተል፣ አቅጣጫ በመስጠት እና ውሳኔዎችን በማስተላለፍ በየአካባቢው ከተቋቋሙ የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ፈጻሚ ማዕከላትን ተግባራት ለመከታተል በመደበኛነት በየሁለት ቀናት እንደሚገናኝ ተገልጿል።
በዚህም የሚኒስትሮች ኮሚቴው በትላንትናው ዕለት መደበኛ ስብሰባውን በሰላም ሚኒሰትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሰብሳቢነት ማካሄዱ ተጠቁሟል።
እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የየዘርፍ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ በቀጣይ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ መሰጠቱን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።