ኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን በ68% ለመቀነስ የያዘችው ዕቅድ ከፍተኛው ነው – አምባሳደር አሌክስ ካሜሩን

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ችግር እየፈጠረ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የካርበን ልቀቷን በ68 በመቶ ለመቀነስ የያዘችው ዕቅድ ከዓለም ከፍተኛው እንደሆነ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ምክትል አምባሳደር አሌክስ ካሜሩን ገለጹ።

በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ እየተከሰተ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ፈተና እንዲሁም ለመጪው ትውልድም እንዲሁ ከባድ ኪሳራ የሚያስከትል እንደሆነ በዩጋንዳ የእንግሊዝ የአየር ንበረት ለውጥ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ካቴ አይሪ ተናገግረዋል።

ምክትል አምባሳደር አሌክስ ካሜሩን አክለውም ይህ ችግር በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣናው እያደገ ለሚመጣው የህዝብ ብዛት የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እና የስራ ዕድል ለመፍጠር እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ባለፈው ዓመት ብቻ በምስራቅ አፍሪካ የዝናብ እጥረት፣ የመሬት መንሸራተት፣ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ጎርፍ እንዲሁም የእንበጣ መንጋ መከሰቱን በኬንያ የእንግሊዝ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጃን ማሪዮት ገልጸዋል።

በሶማሊያ የእንግሊዝ አምባሳደር ካቴ ፎስተር በበኩላቸው ይህ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር በታሪክ የመጀመሪያው ነው ብለውታል።

ይህ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቅረፍ እና ለመቋቋምም አንድ መቶ ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ምክትል አምባሳደር አሌክስ ካሜሮን ጨምረው አስታውቀዋል።