የካቲት 26/2016 (አዲስ ዋልታ) ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የኦዲት ሪፖርት እና ዕቅድ በወቅቱ እና በጥራት እንደማያቀርቡ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር የ6 ወራት የኢንስፔክሽን አፈጻጸምን አስመልክቶ ለፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የውስጥ ኦዲት እና የፋይናንስ ኃላፊዎች ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው ይህንን የገለጸው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተለያዩ ተቀባይነት የሌላቸውን ምክንያቶችን በመፍጠር የኦዲት ሪፖርትና ዕቅዳቸውን በወቅቱ እና በጥራት ባለማቅረባቸው ትልቅ ክፍተት መፈጠሩን በመድረኩ ላይ አመልክተዋል።
ስራን አቅዶ ያለመስራት እና በተገቢው መንገድ ሪፖርት ያለማድረግ አሰራር ሊቀጥል እንደማይገባም አሳስበዋል።
የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደርን ዲጂታላይዝ ማድረግ አንዱ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ ለዚህ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን በጀት እንደሚመድብ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የኦዲት ሪፖርት አቀራረብ በሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስራ አስፈጻሚ በኩል IRMS /Integrated Report Management System/ በሚል ስያሜ በተዘረጋው ዲጂታል ስርዓት በኩል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው መመሪያ መሰጠቱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
በመድረኩ የተገኙት የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የውስጥ ኦዲት እና የፋይናንስ ኃላፊዎች በበኩላቸው ከአደረጃጀት፣ ከአሰራር እና ከዲጂታል ሲስተም ጋር በተገናኘ ያሉባቸውን የተለያዩ ተግዳሮቶች አንስተው በሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ እንደተሰጠባቸውም ተገልጿል።