በቂ ሰዓት ተኝተውም ለምን ይደክማሉ?….

በቂ እንቅልፍ መተኛት

ጥናቶች የሰው ልጅ በቀን ከ7 እስከ 8 ሰዓት መተኛት እንዳለበት ያሳያሉ፡፡ ሆኖም ግን መተኛት የሚገባንን ሰዓት ተኝተንም የድካም ስሜት ተሰምቶን ያውቅ ይሆናል፡፡

በቂ ሰዓት መተኛት ብቻ ጥሩ እንቅልፍ ያስገኛል ማለት እንዳልሆነ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም በቂ ሰዓት ከመተኛት በተጨማሪ ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ከእንቅልፋችን ስንነሳ ድካም እንዳይሰማን ያደርጋል፡፡ ጥሩ እንቅልፍ እንዳይኖረን ከሚያደርጉን ምክንያቶች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

1. ድባቴና ጭንቀት
ድባቴና ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ቶሎ እንቅልፍ አይወስዳቸውም፡፡ እንዲሁም ከተኙ በኋላ በመሀል ብዙ ጊዜ ይነቃሉ፡፡ ይህ በቂ እንቅልፍ ብናገኝም የድካም ስሜት እንዲሰማን ምክንያት ይሆናል፡፡ በመሆኑም በተቻለ መጠን ጭንቀትና ድባቴን ከሚያመጡ ነገሮች መራቅና ደስተኛ ህይወት መምራት ይመከራል፡፡

2. ተኝተን የምንነሳበት ቋሚ ሰዓት አለመኖር

ብዙዎቻችን የእንቅልፍ ሰዓታችንን ስንቀያይር ይስተዋላል፡፡ ለአብነትም ማታ የማምሸትና በእረፍት ቀናችን ማለዳ ላይ ከወትሮው ረፈድ አድርገን የመነሳት ልማድ ይስተዋላል፡፡ ታዲያ ዘውትር በተመሳሳይ ሰዓት ወደ እንቅልፍ አለመሄድ ሌላኛው ከእንቅልፍ በኋላ የድካም ስሜት እንዲሰማን ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡

 

3. አብረውን የሚተኙ ሰዎች

አብረውን የሚተኙ ሰዎች የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው ከሆኑና የሚገላበጡ ሰዎች ከሆኑ እኛ ጥሩ እንቅልፍ እንዳናገኝ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ስለሆነም አብረውን የሚተኙ ሰዎች ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት የእኛ እንቅልፍ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡

4. የተሻለ የእንቅልፍ ከባቢን እና ልምዶችን መፍጠር

የምንተኛበት ቦታ ብርሃን ያልበዛበትና ሙቀት ያልበዛበት ሲሆን የተሻለ እንቅልፍ እንድናገኝ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ከመተኛታችን ከ6 ሰዓት በፊት ቡናና መሰል አነቃቂ ነገሮችን አለመጠቀም እንዲሁም አልኮል መጠጥና ቅመም የበዛባቸውን ምግብ መመገብ በመቀነስ የተሻለ እንቅልፍ እንድናገኝ ይረዳናል፡፡

5. ድካም

የድካም ስሜት በአብዛኛው የሚሰማን ከሆነ ጥሩ እንቅልፍ እንዳንተኛ ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለሆነም የድካም ሰሜት በሚሰማን ጊዜ ከወትሮው የእንቅልፍ ሰዓታችን 1 ሰዓት ቀደም ብሎ መተኛት የተሻለ እንቅልፍ እንድናገኝ ይረዳል፡፡

6. እንቅስቃሴ አለማድረግ

እንቅስቃሴ አለማድረግ ጥሩ እንቅልፍ እንዳናገኝ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት አስፈላጊ ነገር ነወ፡፡

7. በቂ ውሃ አለመጠጣት

በቂ ውሃ አለመጠጣት ከፍተኛ የሆነ የእንቅልፍ እና የድካም ስሜት እንዲሰማን ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ በመሆኑም በቂ ውሃ መጠጣት ሰውነታችን የሚሰማውን የድካም ስሜት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

8. የእንቅልፍ መዛባት

የእንቅልፍ መዛባት ሌላኛው ጥሩ እንቅልፍ እንዳናገኝ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ይህ ችግር ከላይ ከተጠቀሰው ቋሚ የእንቅልፍ ሰዓት አለመኖር ጋር የሚያመሳስለው ነገር ቢኖርም ይህ ግን ከዛም ከፍ ያለ ችግር እንደሆነና የሀኪም እርዳታ በማገኘት የእንቅልፍ መዛባት ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡