የሰላም ሚኒስቴር “ምሳዬን ለወገኔ” በሚል የዓይነትና ገንዘብ ድጋፍ ለአደጋ መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን አደረገ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) የሰላም ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች “ምሳዬን ለወገኔ” በሚል ሀሳብ ከ191 ሺሕ በላይ የዓይነትና ከ1.8 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ለአደጋ መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን አበርክተዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አፈታት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ በተለያዩ ጊዜያት ለችግር ለተጋለጡ አካባቢዎችና ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የአደጋ መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ጀማል “ከተረፋችሁ ሳይሆን ከምሳችሁ ቀንሳችሁ በችግር ውስጥ ላሉ ወገናችሁ ስለደረሳችሁ እናመሰግናለን” ብለዋል።

ሀገሪቱ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ዜጎች ለችግር መዳረጋቸውንና መሰረተልማቶች መውደማቸውን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ ከዚህ ቀደም ይረዱ የነበሩ ለጋሾችም የሚያደርጉትን ሰብኣዊ ድጋፍ ማቆማቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ወገኖቻችን እንዳይቸገሩ ኢትዮጵያ በራሷ ቆማ እንድትታይ ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከራሱ በጀትና ከሠራተኛው በማሰባሰብ በተለያዩ ጊዜያቶች ለመከላከያ ሰራዊት በአፋርና በአማራ ክልል ለተጎዱ ወገኖችና ተቋማት ከ3ሺሕ 325 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገ ታውቋል።

በሣራ ስዩም