ለአዲስና ነባር አምባሳደሮች ስልጠና እየተሰጠ ነው

የካቲት 14/2014 (ዋልታ) አዳዲስና ነባር አምባሳደሮች በተወከሉበት አገር የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ያስችላቸው ዘንድ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከየካቲት 15 እስከ የካቲት 27 በተዘጋጀው የቢሾፍቱው ስልጠና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ዋና ማጠንጠኛ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካ አያኖ አምባሰደርነት በተቀባይ አገር የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው ያሉ ሲሆን አምባሰደሮች በሚየሄዱበት አገር በተለያዩ መስኮች የአገራቸውን ጥቅም ሊያስጠብቁ ይገባል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅቱ የሚፈልገውን ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እውን ለማድረግ ተቋማዊ ለውጦችን ሲያደረግ ቆይቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሸባሪው ትሕነግ በከፈተው ጦርነት ዓለም ዐቀፍ የሆነ ፖለቲካዊ ጫናዎች ሲያድርባነት ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያን ሀቅ ለዓለም በማሳወቅ በኩል ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

አሁን ላይ ዲፕሎማሲው ማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮችን መጠቀም የሚፈልግበት ግዜ በመሆኑ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘርፍ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት ፡፡

መስከረም ቸርነት (ከቢሾፍቱ)